Skip to main content
y

የሌማት ትሩፋት ግብርና የኢኮኖሚ እድገትን ከማፋጠን ባሻገር የህዝቡን የበለፀገ ምግብ አቅርቦት በሟሟላትና የአመጋገብ ስርዓትን በማሻሻል ረገድ የሚሰጠው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው። እንደ ሀገር የሌማት ትሩፋት ግብርና ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት የጀመረው ከለውጡ መንግስት ወዲህ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከተጠበቀው በላይ የአልሚውን ህብረተሰብ ኢኮኖሚ ከመለወጥ አንፃር አስደማሚ ውጤት አስገኝቷል። የሌማት ትሩፋት እንሰሳት እርባታ የስጋና የወተት ተዋፅኦ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በሀገር ደረጃ የአልሚውን ህብረተሰብ ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይ በማድረግ በኩል ፈጣን እድገት ያመጣ ሲሆን የወተት ከብት እርባታ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጓል ። እንዲሁም የከተማው ማህበረሰብ ያለውን ጥቂት ቦታ በመጠቀም ዶሮና እንስሳት በማርባት፥ ንብ በማነብ ፥ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመትከል ከጓሮው በአነስተኛ ወጪ የአልሚ ምግቦች ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል። እንደ ሀገር የሌማት ትሩፋት ግብርና ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጠው ወዲህ የአልሚውን ማህበረሰብ ቁጥር ከመጨመር አንፃር ከፍተኛ እድገት ያሳየ ሲሆን ይህም የወልና የቤተሰብ ኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠን በኩል የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። የሌማት ትሩፋት ግብርና በግለሰብ ደረጃ ፥በማህበር ደረጃና በትላልቅ ካምፓኒና ፋብሪካ ደረጃ ሊመረትና ሊሰራ የሚቻል የኢኮኖሚ ዘርፍ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል። በሌማት ትሩፋት ግብርና ዘርፍ የዶሮና እንቁላል ምርት፥ የማር ምርት ፥ እንዲሁም የወተት ተዋፅኦ ምርቶች. ..ወዘተ በትላልቅ ፋብሪካዎችና ካምፓኒዎች ሊመረቱ የሚችሉ ሲሆን ይሄም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ አቅርቦት የሚውል የኢኮኖሚ ዘርፍ በመሆኑ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው። በተጨማሪም የህብረተሰቡን የአመጋገብ ባህል ከማሻሻልና የበለፀጉ ምግቦች ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር አዲስ የአመጋገብ ስርዓት የሚፈጥር ሲሆን የከተማው ማህበረሰብ አልሚ ምግቦችን ከጓሮው እንዲያገኝ ስለሚያስችለው የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የጎላ ነው። የሲዳማ ክልል የሌማት ትሩፋት ግብርናን ተልዕኦ በማሳካት ረገድ በሀገር ደረጃ ሞዴል ክልል እንዲሆን ያስቻለው ሲሆን፤ የሌማት ትሩፋት ተግባራት ዉጤታማ ማድረግ በአርሶ አደሩና በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጅ የልማት ዘርፍ እንዲሆን በማድረጉ በኩል ያከናወናቸው ተግባሮች ክልሉን ውጤታማ እንዲሆን አድርጎታል።